ኢህአዴግ ጋዝ የነካው ምግብ…

ኢህአዴግ ጋዝ የነካው ምግብ ነው ስንል በምክንያት ነው። የጥቅም እና ዝርፊያ ተካፋይነቱን ሕወሃት የበላይ ሆኖ ቢሰፍርበትም፥ ትናንት ሁሉም በተመቸው እና ጊዜው በፈቀደለት ልክ ዘግኗል፣ አንገላቷል፣ በየፈርጁ እና በየደረጃውም፥ የግፉም የዝርፊያውም ተካፋይ ነበር። የሚደርሰው ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ እንዳይታወቅ በመሸፋፈን ረገድም ሁሉም አባል ይኽ ነው የማይባል ሚና ተጫውቷል። ምንም እንኳን በሕወሃት የበላይነት ቢዘወርም፥ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን እና ንጹሐንን የማፈኑን ሥራም በድርጅት ደረጃ አቋም እና አተገባበር ይዘው ሲያደርጉት የነበረው ነውና፣ የጭንቀት ቀን ሲመጣ ጣት መቀሳሰሩ በኅሊና ዳኝነት ፊት የትም አያደርስም። ማናቸውም አሸባሪውን ድርጅት ሲያገለግሉ እንጂ፣ ገዳም አልነበሩም።

ሁሉም ደርሶ በድል አጥቢያ አርበኝነት ስሜት እና በለውጠኝነት ሽፋን ጣት ቀሳሪ ይሁን እንጂ፣ ለመዛኝ እና ለፈራጅነት የሚያበቃ ንጽህና ያለው ያን ያህል አይደለም። ምንም አያውቅም የሚባለው አባል እንኳን፣ ቢያንስ ዝም በማለት እና ንጹሐን ሲንገላቱ ባለመከላከል፣ ድሀ ሕዝብ ሲመዘበር የምዝበራው አበል ተካፋይ በመሆን እያመሰገነ እና፤ አባል ያልሆኑና ያገባኛል ያሉ ሰዎችን በጠላትነት እየፈረጀ ኖሯል። የኢትዮጵያ አምላክ ራቁት እሲያስቀር፣ የጊዜ ፈረስ እንዲህ በአፍጢም እስኪፈጠፍጥ ድረስ!

በርግጥ፥ አንድም ይሁን ሁለት፣ ያጠፋ ሰው መጠየቅ መጀመሩ አግባብ ነው። ሆኖም ግን፥ የሌላው ነውረኝነት አለመጋለጥ፣ የተጋለጡትን እና በህግ ለመጠየቅ መንገድ የተጀመረላቸውን ሰዎች ጉዳይ ስህተት አያደርገውም። ዛሬ ጊዜው ፈቅዷል፣ ትናንት አልፏል በሚል ቀመር፥ አብረው ሲፈተፍቱ፣ የሕዝብ ደም ሲገብሩ እና ነውሩን ሲጋርዱለት፣ በታማኝነት እና ቁርጠኝነት ሲያገለግሉት የነበሩትን ድርጅት “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ” በሚል ጲላጦሳዊ ግብዝነት ሲነዛ ግን፥ አሁንም ህሊና ካለ ይፈርዳል።

እንደማሳያ፥ ሰሞኑን በድፍረታቸው እና አጋላጭነታቸው ተደንቀን፣ አፋችንን ከፍተን ሀቀኝነታቸውን የመሰከርንላቸውን አምባሳደር ሱለይማን ደደፎን የትዊተር ገጽ በጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰን በመቃኘት ነገሬን ልቀጥል።

አቶ ሱለይማን ዛሬ ፓርቲአቸው ኦህዴድ የበላይ ባይሆን እና ሕወሃት ቢቀጥል ኖሮ፣ ሰጥ ለጥ ብለው የሚገዙ እንጂ “ግፍ አንገፈገፈኝ” ብለው የሚለቁ አይነት ነበሩ የሚያስችል የጀርባ ታሪክ እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ የለም። በርግጥ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች አባላቶችም እንዲሁ ከመጣው ጋር ቀጥለው፣ በጥሎ ማለፍ ድርጅታቸውን እያሽሞነሞኑ ይቀጥሉ እንደነበር መገመትም ከባድ አይደለም። ድርጅታቸው ኢህአዴግን በታማኝነት ከማገልገል ባለፈ፥ ሲያደርግ የኖረውን ነገር በመሸፋፈን እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማሳጣት የተጫወቱት ሚና ብዙ ነው።

በኦክቶበር 2013 የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ መንግስት አዘጋጅነት፣ እነ ኡሁሩ ኬኒያታ የሰው ልጆች ላይ ወንጀል በመፈጸማቸው  በሚል መከሰሳቸውን ለመከላከል፥ በአዲስ አበባ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ነበር። አጀንዳቸውም የዓለማቀፉን የወንጀል ፍርድቤት International Criminal Court (ICC) ለመቃወም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ተገኝተውም ፍርድቤቱን መተቸታቸውን ተከትሎ፥ የአፍሪካ መሪዎችን ስብሰባ ጠርተው ነበር። ነገሩ “ነግ በእኔ”፤ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል” ነበር። በተለይ ደግሞ የነገሩ ጠንሳሽ ኢትዮጵያ መሆኗ “ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም” ዓይነት ነበር።

ታዲያ ያንን ተከትሎ፥ ከሁለት ወይም ከሶስት ሳምንታት በኋላ በኦክቶበር 28 ቀን፥ አቶ ሱለይማን

I am skeptical on the very intention to create the ICC. Why doesn’t it open its eyes on the whole globe than giving excess attention to Africa?

በማለት ለአምባገነኖቹ የአፍሪካ መሪዎች መቆርቆራቸውን ገልጸው ነበር።

1

ኖቬምበር 15 ቀን 2013፥ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ የነበረውን ስቃይ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማውገዝ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ለማካሄድ በጠራው የሰላማዊ ሰልፍ ላይ የወጡ ሰዎች፣ ላይ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፉን በመከልከል ሰዎችን ደብድቦ እና አስሮ ነበር።  ታዲያ በዚያን ቀን፥ አቶ ሱለይማን

Ethiopian Gov’t has allocated 50 million Birr to integrate Ethiopians deported from Saudi Arabia. But what do the opposition parties are doing? Ethiopian opposition parties are trying to benefit out of tears of Ethiopian migrants in Saudi Arabia as usual. Why?

ብለው በሁለት ትዊት ጽፈው ነበር።

2.jpg

በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘቡን የመደበው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ላይ መሆኑን ዘንግተውት እንደልግስና ቆጥረውት ተመጻድቀው ነበር። ገንዘቡ በአግባቡ ይዋል አይዋልም አይታወቅም። ሆኖም ግን፥ በወቅቱ ለወገን በመቆርቆር የተጠራን ሰልፍ ተከትሎ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በጅምላ ለመፈረጅ እና፣ እንደ ኢህአዴግ አባልነታቸው “ተቃዋሚዎች በሕዝብ እንባ ለማትረፍ የሚሞክሩ ናቸው” ብሎ ስም ለመለጠፍ እና፣ “መንግስት ይህን ሲያደርግ፣ እነሱ ግን ምንም እንዳላደረጉ” ለማጉላት ዳክረው እንደነበር እናያለን።

20131115163925420734_20

(እንደፓርቲ ከአባላት ከሚያገኙት መዋጮ ላይ መቋቋሚያ እንዲሰጡ ጠብቀው ነበር ማለት ነው። እንደተቃዋሚ ፓርቲነታቸውም ለዜጎች ጥቃት መቆርቆራቸውንም አቃለዋል።) ከዚህ በላይ ኢህአዴን መጋረድ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቱን መደገፍ ከየት ይመጣል?

እነ ወ/ሮ ሚሚ ስብሀቱ፣ አቤል ተስፋዬ እና መርከብ ነጋሽ ተሳትፈውበት በነበረ “የቀለም አብዮት” ዶክመንተሪ ማግስት፥ የዞን 9 ስድስት ጦማርያን እና 3 ጋዜጠኞች ወዳጆቻችን በአፕሪል 2014 መታሰራቸውን ተከትሎ፥ አቶ ሱለይማን፣ በሜይ 1 2014፥

Zone Niners are messangers of color revolution hired by neo-liberal masters. They are instructed to create violence ahead of next election. Press Freedom is not systematic invasion or campaign to change regime by color revolution. That is what the west are trying in Ethiopia.

ብለው ንጹሀን ላይ ጣታቸውን ቀስረው፣ እና የመንግስትን ጭቆና ለመሸፈን ሞክረው እንደነበርም እናስታውሳለን።

4.jpg

የመንግስትን የተጋነኑ “የኢንቨስትመንት” ወጪዎችን በተመለከተም፥ በዲሴምበር 3፣ 2014

Where will huge state investments lead Ethiopia? Obviously to growth

ብለው ጽፈው ነበር።

6

እንግዲህ ወደ እድገት ያመራናል ያሏቸውን ወጪዎች በተመለከተ ነው፣ አሁን ያላየ፣ ያልሰማ ሆነው በጻድቅ ምስክርነት የቆሙት። ምስክርነት መቆማቸውን መንቀፌ አይደለም፣ ነገር ግን ትህትና የቀላቀለ ቢሆንና፣ ሁላቸውም መነካካታቸውን የማይክድ መንፈስ ያረበበት አነጋገር ቢሆን የሚል የከሸፈ ጉጉት እንጂ።

በሌላ ማሳያ፥ የአሁኑ የጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የያኔው የፍትህ ሚንስትሩ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፥ በ2011

ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ አይታሰርም። ያለፍርድቤት ውሳኔ አይቀጣም። በምርመራ ወቅት ድብደባ የለም። ግርፋት የለም። ሕገመንግስታችን ይከለክላል። እነዚህን ነገሮች ማለት ነው። ስለዚህ እንደዚህ ተደርጓል፣ እንደዚህ ተደርጓል ተብሎ አሉባልታ ካልሆነ በስተቀር በተጨባጭ እንደዚህ አይደረግም። በማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ በምርመራ ላይ የሚገኙ፣ በፍርድቤትም የሚገኙ ማየትም፣ መጎብኘትም ይቻላል። እየተደረገም ነው። በውስጥም በውጭም ባሉት አካላት ነው። በዋናነት ለነዚህ አካላት አይደለም መንግስት እነዚህን ስራ የሚሰራው።

በዋናነት፥ ቅድም እንዳልኩት፣ ህገመንግስቱ ላይ የተቀመጡትን መብቶች የማስከበር፣ የማክበር ኃላፊነት የመንግስት ነው። ይሄም ህግ የወጣው፣ [የዜጎችን] መንግስት ሌት ተቀን እየሰራ ያለው፣ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ነው እንጂ ሌሎች ሶስተኛ ወገን የውጭ አካላትን ለማስደሰት፣ ወይ ደሞ ለማስቀየም አይደለም። ለዜጎች፣ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ፣ በአገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ስር እንዲሰድ ለማድረግ ነው እየተሰራ ያለው እንጂ፤ ለነዛ አካላት ተብሎ የሚሰራ ነገር አይደለምና፣ ጣልቃ የሚገባበት ነገርም አይኖርም።

ባሉበት አንደበታቸው፣ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን አስመልክቶ የሰጡት መግለጫ ላይ፥ ይደርስ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የገለጹበትን መንገድ እናስታውሳለን። ቪዲዮውን እዚህ ይመልከቱ።

የበፊት ንግግራቸው መታወሱ ሲወራ፣ ወዲያውኑ ዋልታ የያኔውን ቪዲዮ ከድረ ገጹ ላይ ወዲያው ያነሳው ቢሆንም፣ ቀድመው ያወረዱት ሰዎች እየተቀባበሉት ተመልክተነዋል። (ዋልታስ ቪዲዮውን ማንሳቱ ምን ይባላል?)

እንግዲህ በደም የተጨማለቀ ስርዓትን በሀቀኝነት ማገልገል እና ሲደርስ የነበረውን ግፍ እና በደል ሁሉ፣ የሰብአዊ፣ የዴሞክራሲ እና የሕገመንግስት ሽፋን በመስጠት እንዳልነበሩ፥ አሁን ሌላው ላይ በሚናገሩት ነገር ህሊና ቢኖር ኖሮ አይሸመቅቅም ነበር ወይ?

ከላይም እንዳልኩት፥ ትናንት እንዲህ ተደርጎ ነበርና ዛሬ ዝም ይባል አይደለም። ቢያንስ ግን፥ ትናንት ተሳትፎ የነበራቸው፥ ከጋዜጠኛ እስከ ባለስልጣን፤ ከተራ አባል እስከ ፈላጭ ቆራጭ ድረስ፥ “ስላልተጋለጥን/ስለማንጋለጥ” በሚል ስሜት፥ ወይም በኖሩበት የአድርባይነት ስሜት፣ ነገሮችን ሲተርኩ፣ ፍጹም ከደሙ ንጹህ መስለው ለመታየት የሚያደርጉትን ነገር በልኩ ቢያደርጉት የሚል ነው። አሁንም ተጠያቂነት ድንበር አይኑረው!

እንግዲህ መመዘዝ የተጀመረው የሙስና እና የሰብዓዊ ጥቃት ክር የት ጋ እንደሚቆም በጉጉት እና በሌሎች በራሪ እንስሳዎች እናያለን! 😉

ዕድሜና ጤና ይስጠን እንጂ ከጊዜ ዳኝነት ማንም አያመልጥም!

ሰላም!

ከማዕበሉ ባሻገር…

እንደሚታየው፥ ሁላችንም በፍስሀ እና በእርካታ፣ በስሜት ማዕበሉ ላይ ጡዝ ፍንጥዝ እያልን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይኽን ያሳየን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው!
 
ሚዲያዎቹም፣ አክቲቪስቶቹም፣ ፖለቲከኞቹም፣ ጋዜጠኞቹም… ሁሉም በአንድ ዓይነት አጀንዳ ተወስዶ፣ በአንድ ዓይነት ግብር ተጠምዶ …ደፈር ብሎ የህግ የበላይነት ይከበር የሚል እና ስለፍትህ የሚጮኽ፤ ስሜታችንን ደርዝ በማስያዝ፥ ለነገ የጋራ ጉዳዮች እንድንዘጋጅ አቅጣጫ የሚጠቁም፤ የንግግር ባህላችን እንዲሻሻል የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያቀርብ፤
 
ቢያንስ ፍቅርን እና አንድነትን በሚያደረጅ መልኩ፥ ድሮ እነ ሂሩት መንግስቴ በ”ከሴቶች አድማስ” በ”ከያቅጣጫው” ዓይነት ፕሮግራሞች ዙሪያ ገባውን ያስቃኙን እንደነበረው፣ የገጠር እና የከተማ ማሕበረ – ባህላዊውን መስተጋብር፣ እና የጋራ እሴቶቻችንን ዓይነት እንኳን በማሳየት፥ የእርስበርስ ትስስራችንን በማውሳት፣ ለውጡን የሚያቀላጥፉ ተግባራትን የሚያደርግ ጠፍቶ፥ ሁላችንም በውዳሴ ላይ የማተኮራችንን ምክንያት ሳሰላስል እኒህን 3 ምክንያት መስለው ታዩኝ።
 
1) አጀንዳውን ሁሉ ኮካዎች ያረክሱታል!
 
በተወሰነ መልኩ ከውዳሴ መስመር ወጣ ተብሎ የሚሰጥ አስተያየት፣ ለሕወሃት ኮካዎች የሰርግና ምላሽ ያህል የሚያስቦርቅ መሆኑን ታዝበናል። በዚህም የተነሳ ምንም ዓይነት አጀንዳ ቢነሳ፣ ምንም ዓይነት ነቀፋ እና ትችት ቢከናወን ‘ይደሰታሉና’፣ ብሎ የመፍራት ነገር አለ። ለዚህ አስተዋጽኦ የሚያደርገው፥ የለውጥ ፈላጊው ወገን መካከል፥ አንዳንዶች ከሌሎቻችን የተሻልን አገር ወዳድ፣ አጋዥ፣ ሰላም እና ለውጥ ፈላጊ መስለን በመታየታችን በምናሳየው የተሟጋችነት እና አፋችሁን ዝጉ ባይነት መታገላችን ነው። ፍሬ ሀሳቡ ቀርቶ፣ ብሽሽቁ ላይ እናተኩራለን።
 
ሆኖም ግን፥ ማገዝ ፈርጀ ብዙ ነውና፣ የተሰራውን በማድነቅ ከመደሰት እኩል (ወይም በላቀ ሁኔታ) ለተራማጅ መንግስት፥ ነቀፋ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
 
2) አሁን ከጊዜው ጋር የሚዜመውን ካላዜምኩ፣ የሚጣጣለውን ካላጣጣልኩ፥ ኋላ ተከታይ/አድማጭ/ተመልካች ባጣስ የሚል ነገር ሊኖርም ይችላል!
 
ሲሆን፥ ማህበራዊውንም ሆነ መደበኛውን ሚዲያ ተከታታዮች ከምንቃኘው ይልቅ፣ ሚዲያው የሕብረተሰቡን ስሜት በመቃኘት ረገድ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል። አሁን እየሆነ ያለው ግን በተገላቢጦሽ ነው። ከሕዝብ ጋር ለመቆም፤ ሰው ስለሚከፋ በሚል፣ በይፋም ባይሆን ውስጥ ውስጡን ማባበል/ማስመሰል/መመሳሰል አለ። ይህም በተለይ የኢመደበኛው ሚዲያ መሰረት አድማጭ/ተመልካቹ ስለሆነ ነው። በዚህ የተነሳ፣ ደፈር ብሎ ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነቱን ለመጠቀም የሚሞክረውን ሳይቀር በማሸማቀቅ የምንጫወተው አሉታዊ ሚና አለ። ስድብ አስታጥቆ በብሎክ የሚያሰናብተውም ብዙ ነው።
 
ይህ ደግሞ ጭራሽ የለውጡን ጽንሰ ሀሳብም የሳተ ነው!
 
3) ፍቅራችን እና ፈንጠዝያችን መሰረት ያደረገው፥ ምሬትና ጥላቻን እንጂ፣ እውነተኛ የለውጥ ፍላጎትን አይመስልም! ስለዚህም፥ ስለምንነቅለው እንጂ ስለምንተክለው ነገር ቸልተኞች ነን።
 
ይህንን ለማለት ያስደፈረኝ፥ ገና ካሁኑ የሰለቹን ነገሮች በዝተው በማየቴ ነው። ገና ካሁኑ ትናንት ከሕዝብ ጋር ሆነው ድምጻቸውን በማሰማታቸው ክብርና ተቀባይነትን ያተረፉትን ሀጫሉን እና ቴዲን በራሳችን የልብ ምት መዝነን “ዐይናችሁ ለአፈር” ለማለት በመውተርተራችንም ፍንትው ብሎ ይታያል። አምባገነኑን ኢሳያስን ባቆላመጥንበት ዕለት እና መድረክ ላይ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያስገምተናል። እንደሚነዳ ፍሪዳ ለዛሬው የስሜት ነውጥ መስዋዕት ልናደርጋቸው ስንንጋጋ ፍጹም ቅሬታም ያለብን አይመስል። ስንደመር ለመቀነስ የምንሯሯጠው ነገር ብዙ ነው።
 
ይህችን አንጻራዊ ሰላም እና ነጻነት ለማግኘት የፈሰሰውን ደም፣ የጠፋውን ሕይወት፣ የተዘጋውን ልሳን፣ የተሰደደውን ሕብረተሰብ፣ የጎደለውን አካል፣ የጨለመበትን ሕይወት፣ የወረደውን እንባ በማጣጣል ውስጥ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደምንችል እንጃ።
 
ባለፈው “ቀሪ የፖለቲካ እስረኞችም ይፈቱ” ሲባል፥ “ኸረ ባካችሁ ዘንድሮም እስረኛ ይፈታ ፖለቲካ ላይ ናችሁ። ተደመሩ” የሚሉ አፍላ ካድሬዎች አይተን በግነናል። ሶማሌ ክልል ውስጥ ሕዝብ ሲያልቅ፣ ጌዲኦ ተፈናቅሎ ሲያልቅ፣ ሀዋሳ እርሰበርስ ተባልቶ ሲያልቅ፥ ካፉ ቃል ሳይወጣ በፌሽታ ውስጥ የነበረ “ቂሊንጦ እስረኞቹ አመጹ” ሲባል፣ “ለምን እርምጃ አይወሰድም” ሲል ታዝበናል። ሰው በላው አብዲ ኢሌ ጌታቸውን አማው ብለን “ጀግና” ሲባል ሰምተን “ቦ ጊዜ ለኩሉ” ብለን ተገርመናል።
 
(የሆኑት ነገሮች ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ ፕሮፋይል ምስል የሚያስቀይሩ፣ ዘመቻ የሚያስደርጉ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ትናንት ያስተላለፉትን የማረጋጋት ተግባር፥ ቀደም ብለው በማድረግ በመካከል የጠፉት ሕይወቶች የመትረፍ እድል ነበራቸው) የኢትዮ ኤርትራ ሰላም ወሬ እንኳን ገና ካሁኑ የሰለቸው አለ።
 
ቸልተኝነታችን ዋዛ ቢመስልም፣ ውሎ አድሮ ስር ከሰደደ አሳሳቢ ነውና እስኪ ሀሳብ እንጨዋወትበት!
 
ሰላም!