ለአገሬ የህክምና ባለሞያዎች

በአስተዳደር በደል ምክንያት እጀ ሰባራ ለምትደረጉ፣
 
በsterilization መሳሪያ እጥረት ወይም በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ጉልቻ ጥዳችሁ መሳሪያ ትቀቅሉ ዘንድ ለተፈረደባችሁ
 
ደም ለግሳችሁ ነፍስ ለማትረፍ ለምትተጉ
 
በላቦራቶሪ እና በዘመናዊ ዶክመንቴሽን ችግር ምክንያት የምርመራ ውጤት ለሚዘበራረቅባችሁ
 
የሀሰት ሪፖርት እንድትልኩ ለምትጠየቁ
 
በምንም ውስጥ ብዙ ተስፋ ለምትሰጡን፣ ስናያችሁ ብቻ ቀለል ለሚለን
 
ግራ ቢገባችሁ እና ምታደርጉት ብታጡ በእጃችሁ ዳብሳችሁ አይዞህ ለምትሉ
 
ችሎታ ሳያንሳችሁ፣ በስራ ቦታ አለመመቻቸት እና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት የተነሳ አቅመ ቢስ ለምትሆኑ፣
 
አቅመ ቢሱን ካርድ አውጥታችሁ ለምታክሙ፣ መድኃኒት መግዣ ለምትሰጡ (ከፋርማሲ ጓንት ስትገዙም አይቼ አውቃለሁ)
 
በሙስና እና ብልሹ አሰራር ባለሀብቶች ባቆሙት የግል ሆስፒታል ውስጥ ይህን አርጉ ይህን አታርጉ ትንሽ ብላችሁ ለምትሰቃዩ
 
እኛ ሰው ለመጠየቅ ወይ ለህክምና ገብተን እስክንወጣ በሚጨንቀን የሚሸት ሆስፒታል/ጤና ጣቢያ ውስጥ ውላችሁ ለምታድሩ
 
በውሃና መብራት መቆራረጥ ምክንያት ትንፋሻችሁ አብሮ ለሚቆራረጥ
 
ቾክ እንደ መድኃኒት እየታሸገ እና ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት በኮንትሮባንድ ይገባ ዘንድ በየእርከኑ ያሉ ባለጊዜዎች ተባብረው፣ የምታዙት መድኃኒት ታማሚውን ሳያሽል ሲቀር ለምትዘለፉ
 
በተፈጥሮ በሆነ ችግር በተከሰተ ጉዳይ ነፍስ ለማትረፍ ስትረባረቡ ባለጊዜ፣ ሽጉጥ ለሚመዝባችሁ (ከአንድም ሶስት ታሪክ አውቃለሁ። አንዱ በዐይኔ ያየሁት ነው) እልህ በማጋባት ወይም በማስደንበር ሊፈጥር ስለሚችለው ችግር ሳይጨነቅ፣ እያሳየ ሚያስፈራራም አለ።
 
በሽታው በየቅያሱ በሰው እጅ ለሚፈጠርባችሁ። (ጀሶ እና ሳጋቱራ ከመብላት ይጀምራል)
 
በተለይ ከመዲናዋ ከአዲስ አበባ ውጭ ለምትሰሩ፣ ሰርታችሁ ለምታውቁ!
 
ክብር ለእናንተ!
 
በበረሀ ላይ እንዳለ ዛፍ፥ ጥላና ተስፋ ናችሁ።
 
ሕይወት እንደነበር፣ ሕይወት እንደሚቀጥል ማሳያ ምልክቶች ናችሁ።
 
በተለይ የአሜሪካ ሀኪሞችን እና የህክምናውን ሁኔታ ባየሁ ቁጥር ልቤ ስለአገሬ ነዋሪ እና ስለ እናንተ ትደማለች። በእናንተ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፣ ግማሾቻቸውም survive ማድረግ ይችላሉ ብዬ አላስብም። የድሀ አገር ሰው መሆን ደግነቱ ጠንካራ ቆዳ ይሰጣል።
 
በምንም ውስጥ ሁሉንም ሆናችሁ የመኖራችሁ ነገርም እየደነቀኝ፣ ለእናንተ ያለኝ አክብሮት እና ፍቅር ይጨምራል። ልታከም የሄድኩበትን ጉዳይ ድኜ፣ ድብርት እና የጥፋተኝነት ስሜትን እታመማለሁ።
 
የእውቀት ችግር አለባችሁ እንዳይባል፣ ከማንም እንደምትሻሉ በየሰው አገሩ የወጡ የሞያ አጋሮቻችሁ ምስክር ናቸው። እንኳን ሀኪም፣ በየትኛውም ዘርፍ ላይ ኢትዮጵያዊያን ከማንም አያንስም። አንገት አያስደፋም።
 
ይህንን ስል የግል የጠባይ ችግር ያለባቸውን ሁሉ አካትቼ አይደለም። ዳሩ ግን መልካም ስርዓት ቢኖር ኖሮ፣ በወል ከመጠራት ይልቅ እነሱንም ተጠያቂ ማድረግ ይቻል ነበር።
 
አቅም ካገኘሁ ከሀኪም ጓደኞቼ ጋር በነበረኝ ውሎ የታዘብኩ የሰማኋቸውን፣ በአንድ ዓመት የሆስፒታል ሥራ (በፐብሊክ ኸልዝ) ቆይታዬ ያየሁ፣ የሰማሁ የታዘብኳቸውን፣ የማስታውሰቸውን ጥቂት ታሪኮች ለመጻፍ እሞክራለሁ።
 
ዛሬ ግን ይኽችን መጫሬ፥ አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ሀሳቤ ከእናንተ ጋር ነው ለማለት ነው!
 
ዛሬ ድንግዝግዝ ቢሆንም፣ ሲነጋ ብርሃን ይሆናል።
 
ትግላችሁ ለሰፊው ሕዝብ የተሻለ ህክምና ለማስገኘት እና፣ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው በማስቻል ትውልድ የሚያጣጥመውን መልካም ፍሬ ያፈራልና ዛሬ በብዙ ብትደክሙ፣ ብትዘለፉ፣ የሚዲያ ዘመቻ ቢደረግባችሁም አይዟችሁ!
 
መንግስት ሰብስቧችሁ እናንተን አንኳሶ እና ‘ስለህክምና ቱሪዝም የማታስቡ’ ብሎ ተሳልቆ፣ ወላድ እናት ደም የነካው ጨርቋ እንዲታጠብላት መብራት እና ውሃ በሌሉበት ከተማ፣ አዲስ አበባን አስውባለሁ፣ “ወንዞቿን አጥባለሁ” የሚል የ”ቂጥ ገልቦ ክንብንብ” ስላቅ ቢያደርግም፣ አይዟችሁ።
 
እኛንም አትፍረዱብን! ስንመጣ የምናየው የእናንተን ፊት ነውና ስላለው ቁም ስቅል፣ ስለ ህክምና ቁሳቁስ እጥረት፣ ስለሙስናው፣ ስለሕይወታችሁ ባንድረዳ ይቅር በሉን።
 
ጂጂ እና ቴዲ አፍሮ ከጋሪሰን ሃውክ ጋር ከተጫወቱት ሙዚቃ ላይ፣ በእነዚህ የጂጂ መስመሮች ላብቃ!
 
“በቀን በቀን የሚያኖረኝ
ተስፋ ሳልቆርጥ የሚያውለኝ
ዕምነቴ ነው ያለኝ ብርታት
ተሥፋ አልቆርጥም
ተሥፋ አትቁረጥ
አይፈራም አይፈራም
ጎበዝ አይፈራም
ተሥፋ አይቆርጥም”
 
ቴዲም እንዳለው
 
“ሀሳብ አይሆንም አይባልም
ከሀሰብኩት እደርሳለሁ”
 
ካሰባችሁት ደርሳችሁ ለወገን የህክምናውን ዘርፍ ለወገን እና ለአገር እንዲጠቅም ታሻሽሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ!