ስለ24 ዓመቷ ሌንሴ ኔሜ ሹመት

 

43371204_2460431533973313_7357390166161358848_n

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ (CEO) ተደርጋ የተሾመችውን፣ የ24 ዓመቷን ሌሊሴ ኔሜ በተመለከተ መረጃውን ማጋራታችንን እና ነገሩን ማውገዛችንን ተከትሎ፣ በግራም በቀኝ ወዳጆች አስተያየት ሰጥተዋል።

 
ነገሩ ያስቆጣቸው በርካቶች የመኖራቸውን ያህል፣ በገራገርነት ተመልክተው “ከቻለች ምን ችግር አለው? ወጣት ወደ ሀላፊነት ሲመጣ ማበረታት ነው ያለብን” ዓይነት ሀሳብ የሰጡም አሉ።
 
ከዚያም አልፈው፣ ጽሁፉ ኦሮሞ ስለመሆኗ በማይገልጽበት ሁኔታ፥ “ገና ለገና ኦሮሞ ስለሆነች፤ የኦሮሞ ስም ስላላት” ብለው በልባቸው የሚያስቡትን (ምናልባትም እየሆነ ያለውን ስለሚታዘቡ) የተናገሩም አሉ።
 
ባረጀ ባፈጀ ማሸማቀቂያ “ኦሮሞፎቢያ” ያሉም አሉ። እንደዚህ እያልን እውነትን የምናፍንበት እና የምናሳቅቅበት ጊዜ ሳያልፍ አልቀረም። ስለኦሮሞነቷ ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ፣ “ከእሷ የተሻለ ለቦታው የሚበቃ ኦሮሞ ስለሌለ ነው ወይ?” ብሎ መጠየቅስ አይቀልም ነበረ? 
 
አሁን ማንሳት የፈለግኩት ግን ነገሩን በበጎ ተመልክተው “ምን ችግር አለው? ዋናው ብቃት ነው እንጂ ዕድሜ አይደለም። እስከቻለች ድረስ ትሁና።” ያሉትን ነው።
 
በመጀመሪያ እንደዚህ ያለ አገር አቀፍ ዋና ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀላፊ (CEO)
መሆን ከልምድም ከእውቀትም አንጻር የሚጠይቀው ብዙ ነገር አለ። የነገሩን ትርጓሜ፣ የሚሰጠውን ሀላፊነት እና ዓለም ላይ እንዴት ነው የሚስራበት የሚለውን መፈተሽ ተገቢ ነው።
 
ብስለት እና አመራር ጋር ሲመጣ፣ ዕድሜ ቁጥር ብቻ አይደለም። የሚያሸክመው ልምድ፣ እውቀትና ብስለትም አለው። 24 ዓመት ተለዋዋጭ ፍላጎት እንኳን ጠርቶ ቦታ ይዣለሁ የማይልበት፣ ከራስ ጋር ተስማምተው የማይጨርሱበት ዕድሜ ነው።
 
እንደዚያ ባይሆን እንኳን፣ ከተመረቀች 2 ዓመት የሆናትን ወጣት ለዚህ ቦታ ለመሾም፣ መስፈርቱ እሷ የምታሟላውን ያህል ብቻ ሲሆን ነው። ካልሆነ ግን ቢያንስ ያስተማሯትም አሉና፣ የት ባሳየችው የአመራር ብቃት ነው ተመራጭ ሆና ለሹመት የምትበቃው?
 
(በርግጥ የሌንሴ የሹመት ሙስና እና ፖለቲካዊ አድልዎ የጀመረው ከዩኒቨርስቲ ከመመረቋ በተሰጣት ሹመት ነው። እንደዚያም ሆኖ እንኳን፣ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የማስተማር ስራዋን ሳትተው፣ ዋና ስራ አስኪያጅነቱን ደርባ መስራት መቻሏም ሌላ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። ካልተሳሳትኩ፣ የስራ አጡ ቁጥር ባሻቀበበት አገራችን ላይ፣ ሁለት የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ መስራት በህግ የተከለከለ ነው። በዚያም ላይ በእንደዚህ ያለ ከፈተኛ የአመራር ስራ ላይ ያለ ሰው፣ መኪና የመንዳትን ስራ እንኳን ደርቦ እንዳይሰራ ጥንቃቄ ይደረግለታል።)
 
ቦታው የተሰጣት በሹመት ነው እንጂ፣ ማስታወቂያ ወጥቶ ሰዎች አመልክተው፣ በነጻ ተወዳድረው እና በገለልተኝነት ተመዝነው አለመሆኑ ነገሩን ከብቃት እና ከእውቀት ጋር እንዳናያይዘው ያደርገናል። ምናልባት እርሷ የትምህርት ቤት ጓደኞች መካከል (የዛሬ 2 ዓመት የተመረቁ) የመጀመሪያ ስራ እንኳን ይዘው የማያውቁ ይኖሩ ይሆናል። በጣም ችሎታ እያላቸው፣ በፓርቲ ተሳትፎ እና ትውውቅ የተነሳ ስራ አጥተው ባክነው የቀሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል።
 
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ “ከቻለችው ምን ችግር አለው? ዋናው መስራቷ ነው” የሚሉት አስተያየቶች ናቸው፣ ሌላ ትኩረቴን የሳቡት።
 
ታዲያ ትናንትና “የትግራይ የበላይነት ነገሰ” ያልነው ለምን ነበር?
 
አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ከጥበቃ እስከ ሀላፊ ድረስ ትግሬዎች ናቸው የሚቀጠሩት እና ቦታ ቦታ የያዙት የተባለው ለምንድን ነው?
 
ኮንዶሚነም ቤት እስከከፈሉ ድረስ ቢሰጣቸው ምን ችግር ነበረው?
 
የጥበቃ ሰራተኛው እስከጠበቀ ድረስ ትግሬ ሆነ ምን ሆነ ለምን ደነቀን?
 
የመከላከያ ሰራዊቱ ብሔር ስብጥር ለምን አሳሰበን?
 
የአውሮፕላን አስተናጋጇ እስካስተናገደች እና አውሮፕላኑ ስራ እስካላቆመ ድረስ፣ ትግሬ ሆነች ምን ሆነች ምን አገባን?
 
መርካቶ ንግዱ እስካልታጎለ ድረስ፣ ጉራጌዎችን አፈናቅለው በግብር እና በኮንትሮባንድ ደግፈው ትግሬዎችን ቢያስፋፉ ምን አስጨነቀን?
 
የተለያዩ ሀላፊነት ቦታዎች ላይ የተሾሙትስ አለመቻላቸው በምን ታወቀና ነው ትግሬ መሆናቸው ያስከፋን?
 
ታዲያ ድካማችን ሁሉ ለምን ነበር?
 
አገሪቱ ላይ ሁሉም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ይሁን ከሚል ቅንነት አይደለምን? ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲነግሱ፣ የዘመድ እና የካድሬ አሰራር እንዲወገድ አይደለምን?
 
“አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ” የሚለው ሙዚቃ ትዝታ ይሁንልን! የትናንቱን የጠላነውን፣ በአዲስ ዛሬ ለመተካት አይደለም ተስፋ እና ጉጉቱ!
 
ኢፍትሀዊ አሰራር ይውደም!

Leave a Reply