የማኅበረሰብ ድረ ገጾች ቆይታችን ትርፍና ኪሳራ

 

ከአዲስ ነገር ጋር የመተዋወቅ መዘዝ12270417_863573420430359_1988740496_n

ብዙ ጊዜ፥ ብርቅ የሚሆን ነገር እጅ ላይ ሲገባ ይዞ የሚመጣው የተለየ አባዜም ይኖራል። ለምሳሌ: ቴሌቪዥን ከስንት አንዱ ቤት የሚገኝ ብርቅ የነበረ ጊዜ፥ ቴሌቪዥን ባላቸው ቤቶች ዘንድ፥ ቴሌቪዥኑ የሚያገኘው እንክብካቤና፣ ለመመልከት የሚሄዱ ህፃናት የሚያዩት አበሳ አይዘነጋም። ቲቪው ይወለወላል፣ እንደሌማት በዳንቴል ይሸፈናል፣ እየታየ ‘ሞቀ አልሞቀ’ ተብሎ ትኩሳቱ ይለካል፣ ቅልጥ ባለ አጓጒዊ ፕሮግራም መሀል… ቆይ ‘ይቀዝቅዝ’ ይባልና ይጠፋል። (እነሱ እንዴት አይጓጉ እንደነበር ይገርመኛል?) ከሚጠበቀው ፕሮግራም ቀደም ብሎ የጎረቤት ህጻናት ቤት በማፅዳትና በመላላክ ያግዛሉ…. ሌላም ሌላም፤ አጀቡ ብዙ ነበረ።

የማቀዝቀዣ (fridge) ቴክኖሎጂ ትውውቅ ብርቅ የነበረ ጊዜ፥ “ኡፍ እንዴት ይሞቃል? እስኪ የፍሪጁን ቁልፍ ስጪኝ አየር ልቀበል” ሳይባልም አልቀረም። ተንቀሳቃሽ ስልክ የተዋወቀ ጊዜም፥ በሰልፍ የተገዛችው ‘ዳስተር’ ስልክ ወገብ ላይ ሻጥ ተደርጋ ስንቱ ላይ ተሸለለ? ስንት ተማለለ? ስንቱ ተንጎማለለ? የሀብትንና የማንነትን ደረጃስ አልመተረም? የስልክ ቀፎ ብርቅ ሲሆንስ፥ ስንት ቀፎ ተገላበጠ? – ሲሆን በእጅ፣ ሲቀር በዐይን። ፌስቡክ ብርቅ የነበረ ጊዜ፤ ማለቴ አሁን… ብርቅ ስለሆነ ሰዉ በየቦታው “ፌስቡክ ከፍቼ…” “ፌስቡኬ ላይ…” ይባባላል። አማራጭ የወሬ ምንጭና ማስተላለፊያ ሆኖም ያገለግላል።

ከዚህ ቀደም የስነጽሁፍ ባለሞያው ቴዎድሮስ አጥላው “ስለ ፌስቡክ እና የኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ያስተዋልኩት” ብሎ በሰየማት መጣጥፉ ላይ፥ “ፌስቡክ በአጭሩ በእያንዳንዱ የህይወታችን ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የምናስገባው፣ ወይም ጣልቃ ገብቶ የምናገኘው ዓለም ነው፡፡ አቋማችንን፣ የመጻፍ ብቃታችንን፣ ቁንጅናችንን፣ ጭንቀቶቻችንን፣ ደስታዎቻችንን፣ ድንፋታዎቻችንን፣ ሽሙጦቻችንን፣ ነቆራዎቻችንን፣ የስታይል ምርጫዎቻችንን፣ የውሸት ማንነቶቻችንን፣ ማስመሰላችንን፣ ቅን አሳቢነታችንን፣ ዋልጌነታችንን፣ ሃይማኖታችንን፣ ዘረኝነታችንን፣ ገርልፍሬንዶቻችንን፣ ልጆቻችንን፣ ሚስቶቻችንን፣ የሚያስደንቁንን፣ የሚያስቁንን፣ … ወዘተርፋችንን ሁሉ በግልጽም ይሁን በስውር የምናሳይበት ዓለም ነው፡፡” ብሎ ገልጾት ነበር።

የselfie (በራስ እጅ የተነሳ የራስ) ፎቶ ብርቅም አለ (የተለያዩ አገራት በአንሺዎቹ ላይ የሚደርሰውን የአደጋም ሆነ፣ ሌሎች አገራዊና ማኅበራዊ ስጋቶች በመግለጽ፥ ሰልፌ መነሳትን የሚከለክሉ ህጎችን እየደነገጉ ነው።)፤ ደግሞ አለ… – የsmart phone (የዜንጦ ስልክ) ብርቅ። ሰዉ ሁሉ ፎቶ እያነሳ፣ ቪዲዮ እየቀረፀ የመዘገበውን ወደ ማኅበረሰብ ትስስር ገጾች ጎራ ብሎ ያጋራል። እየጨሰና እያጨሰ ለጓደኞቹ ያሳያል። የኢንተርኔት፣ የselfie እና የቀፎ ብርቅነት ባንድ ላይ ገጥመው፥ ከኮልኮሌ እስከ ረቂቅ ፎቶና ቪዲኦ የማኅበረሰብ ትስስር ገጾችን ስለሞሉት፣ ነባር ተጠቃሚዎችን ወሰድ መለስ ያደርጋቸዋል።

መቼም የእኛ ሰው፥ መቅረጹን ይቻል እንጂ፣ ይቀረፅለት እንጂ… ስልኩ ባትሪው አይለቅበት እንጂ… ኔትዎርኩ አይጥመምበት እንጂ… ሰዉ እንዳያያዙ፥ አቦሬውንም ምኑንም ያየ ያሰበውን ሁሉ ቀርፆ፣ ፎቶ አንስቶና በቃላት አቀናብሮ ሳያጋራም አይቀር። ሆኖም “ሰርዶ ኃይለኛ ንፋስን አጎንብሶ ያልፋል” እንዲባል፥ የነገሮች ወረትና መዘዞቻቸውን እስኪያልፍ ድረስ ባላየ ለማለፍና ድፍርሱ እስኪጠራ፥ ለተወሰነ ጊዜ ራስን ገለል ለማድረግ የታደሉ፣ ብዙ ቆይተው ብዙ ማትረፍና ብዙ ማስተረፍ ይችላሉ።

ፌስቡክ ነፍስ ነገር

የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች የሰው ልጆችን በማቀራረብ ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚና ትልቅነት ተንታኝ አያሻውም። ተጠቃሚዎቹም ሀሳባቸውን በደግነትና በነፃነት እንዲያካፍሉ ረድቷቸዋል። የማያቋርጠው የፌስቡክ ’what is in your mind…?’ ጥያቄውን በመመለስ ሰበብም አህምሮአቸውን ለመረዳት እና ሀሳባቸውን ለመግለፅ የሚሞክሩ ብዙ ናቸው። ሰዎች በፃፉት ነገር ላይም ሀሳባችንን እንሰጣለን። ከዚህም ባሻገር አገርን፣ ባህልና ችሎታን ከማስተዋወቅና ለሌሎች ከማጋራት አንፃርም የማህበራዊ ትስስር ገጾች ያላቸው አስተዋፅኦ ይህ ነው አይባልም። በማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች ብቻ የሚተዋወቁ ሰዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው፣ ከወዳጅነት አልፈው ብዙ ነገር ሲሰሩ፣ ወዳጅነታቸውን ሲያጠነክሩ ተመልክተናል።

በተለይ እንደ እኛ አገር ባሉ የነጻ ሚዲያ እጥረቶች ላሉባቸው አገራት ነዋሪዎች፥ ከፌስ ቡክ መራቅ እንደ መታፈን ነው። ማረከ አልማረከ፣ ጣፈጠ አልጣፈጠ፣ ታየ አልታየ… ሳይሉ እንደልብ የሚሆኑበትን ቦታ በገዛ ፈቃድ ትቶ መራቅ መወሰን፣ልሳንን በራስ ፈቃድና እጅ የመዝጋት ያህል ጨቋኝ ውሳኔ ነው። በተለይ የሚናፍቁትና የሚያጎድል ብዙ መኖሩን ሲያስቡ ጭቆናው ይበልጥ ገንኖ ይታያል። ያም ሆኖ መገለሉ የሚሰጠው የጥሞና ጊዜም አለና በዚህ ወቅት የተዘጉብን ልሳናት ናፍቆት እንደ አዲስ ይቀሰቀሳል። በሌላ ሰው ጉልበትና ሀይል የተዘጉ ልሳናትና የታፈኑ አንደበቶች ጉዳይም ከማኅበረሰብ ትስስር ገጾች በራቅን ጊዜ ይበልጥ ይገናል። ቢሆንም፥ ቆይተው መጥተው “በአዲስ መልክ ስራ ጀምረናል”ን ሳያስነግሩ አሰላለፍ የሚቀይሩ ብዙ ተጠቃሚዎች አሉ።

ፌስቡክ ስንቱን ጉድ የማሰማቱን/የማሳየቱን ያህል፣ ብዙ ጉድ ጋርዶልናል። ብዙ ቀዳዳ ሸፍኖልናል። በብዙ የመከራ ቀናት ተጠቃሚዎቹን እርስ በርስ አጽናኝ ተጽናኝ አድርጎ አስተዛዝኗል። ከብዙ ዓይነት ሰዎችና ጉዳዮች ጋር አቀራርቧል። ብዙ ዓይነት ችግሮች እንዲቀረፉ አግዟል። ብዙ ሰዎችን ለመታዘብና፣ ማንነትን ለመፈተሽ ፌስቡክ ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። ሰው ሲመጣ፣ ሰው ሲሄድ አብሮ ሀሳብ ይመጣል፣ ሀሳብ ይሄዳል። ልማድ ይረሳል፣ ልማድ ይተካል። ፀሀፊዎች ይታሰሩ ይሆናል፥ ጽሁፍን ግን ማን ችሎ ያስራታል? እውነት ተናጋሪዎች ይጉላሉ ይሆናል፥ እውነትን ግን ማን ያገኛታል? ጩኸቶች ቢታፈኑስ፥ ልሳናት ላይ ማን ይሰለጥን ዘንድ ይችላል? ስጋ ቁም ስቅሏን ብታይ፥ ነፍስን ግን ማን ያገኛታል? ታዲያ ለታፈኑ ድምጾች፥ ፌስቡክ ነፍስ ነገር ነው። የ’cyber’ ዓለም እስትንፋስ ሰው ኖረም አልኖረም ጽዋው አይሞላምና አሰራርና ሰራተኛ እየቀየረ ወደፊት ይጓዛል።

በፌስቡክ ብዙ ዓይነት የማስተባበር ስራዎች ተካሂደዋል። ከቀልብ ማሰባሰብ እስከ ገንዘብ ማሰባሰብ ድረስ የደረሱ ቁም ነገሮች ተከናውነዋል። እንደውም እንደ እኛ ባሉ ሀገራት የአጠቃቀማችንም ችግር ተጨምሮበት እንጂ፥ ከጠቀመንም በላይ ይጠቅመን ዘንድ በተቻለው ነበር። ፌስቡክ ባይኖር የሚዳፈኑ ጉዶች፣ ፌስቡክ ባይኖር የማይጻፉ ጽሁፎች፣ ፌስቡክ ባይኖር የማይሰሙ ድምጾች፣ ፌስቡክ ባይኖር የማይታዩ መልኮች፣ ፌስቡክ ባይኖር የማይዘጋጁና የማንታደማቸው መድረኮች፣ ፌስቡክ ባይኖር ተከብረው የሚኖሩ ቀላሎች፣ ፌስቡክ ባይኖር ተዘንግተው የሚኖሩ ክቡዶች፣ ፌስቡክ ባይኖር እንኳን ሰው ባለቤቱም ሳያውቃቸው ይቀሩ የነበሩ የፈጠራ መልኮች… ወጥተዋል። ሰዉ ያለበት የማሳየት አባዜ የማሳያ ሜዳው ሲኖር ይበልጥ ይበረታልና ብዙ አይተናል። ብዙም አሳይተናል።

የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች እኩይ አጠቃቀም መዘዞች

በ140 ፊደላት በተለይ ትኩስ ትኩሱን ከሚቀነበበው ትዊተር አንስቶ፣ ከርሞም የሚላመጠውን ሽንጣም ሽንጣሙን ለማጋራት እስከሚፈቅዱት ድረ ገጾች፥ ወግ፣ ግጥም፣ ልብ ወለድ፣ ሙዚቃ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትንታኔዎች፣ እስፖርቱ፣ ጡዝጦዛው ሁሉም በያይነት ዓይነቱ ከሞላባቸው የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች፥ እንኳን ሊበሉ ሊታዩም የማይበቁም ሞልተዋል።

አጠቃቀም ካላማረ ግልብነቱም የዚያን ያህል ነው። አንዴ ማኅበሩን ለተቀላቀለ ሰው ኢንተርኔት ባለበት ቦታ ላይ የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች በቀላሉ መገኘት ከመቻላቸው (accessibility) ጋር ተያይዞ ጉዳዮቻችንን እንደፃፍናቸው (እንደወረዱ) እንድናጋራ ስለሚያረገን፥ ቢያንስ እኛ ጋር ቆይተው እንዲበስሉ አንፈቅድላቸውም። ከዚህም ሌላ ይሆናሉ ያልናቸውን ስናጋራ የሚኖሩ አስተያየቶችም አንዳንዶቻችንን ወደኋላ ስለሚጎትቱን፥ ሁሉን ነገር የማጋራት አባዜ ውስጥ ይጥለናል። በመሀሉም ምስጢርና ቁም ነገር ይላላሉ። መብሰልና መለወጥ ይጠፋል። መከባበር ትቀጥናለች። ግልብ ሆነን ላይ ላዩን እንኖራለን። አካባቢያችንንም በአግባቡ እንዳንመለከትና ነገሮችን እንዳንመረምር እንጋረዳለን። የlike እና የcomment ገቢ ያሰክረንና እርስበርስ እንሻኮታለን። ከእኛም አቅም ገጽታችንን ለመገንባት የወዳጆቻችንን ገጽታ እናፈራርሳለን። ታዲያ በዚህ ግርግር መሀል የምንናገረው አብዛኛው ነገር ከ’ብዬ ነበር’ ያለፈ ውጤት ላይኖረው ይችላል። በዚህ የተነሳም ረክተን የተግባር ሰውነታችን ተፈትኖ ይወድቃል።

በርግጥ ፀሀፊው ነፃነቱን ተጠቅሞ የፃፈውን አንባቢውም ነፃነቱን ተጠቅሞ ባተረፈበት ልክ አስተያየቱን ቢሰጥ አግባብ ነው። እኛ የሚሰጠውን አስተያየት የምንመለከትበት ዐይን ግን የራሳችንን መንገድ ብሎም የሀሳብን ነጻ ፍሰት እድገት ይወስነዋል። ያም ሆኖ ግን አንባቢው የሚመለከተው ችግር እያለ፣ እየጎረበጠ፣ ቅር እያለ….ባለበት ሁኔታ ላይ ችግሩን ደፍሮ መጠቆም ባይችል እንኳን በከንቱ ቢያወድስ የተሻለ ማደግ የሚችል ወዳጁን ያቀጭጨዋል።

ባለፈው ዓመት በተደረገ አንድ ጥናት ላይ፥ ከአልኮል መጠጥ፣ ጣፋጭ ምግቦች፣ የዜንጦ ስልኮች (smart phone) እና ሌሎች መዝናኛዎች መካከል ምረጡ ከተባሉ የአንድ መስሪያ ቤት ሰራተኞች መካከል፥ 90 ከመቶ ያህሉ ስልኮቻቸውን መርጠው እንደነበር ታውቋል። ከነሱ መካከል 35 በመቶ ያህሉ ደግሞ፥ ለተወሰኑ ሰዓታት ስልኮቻቸውን ካልያዙ ራቁት የመቆም ያህል እንደሚሰማቸው ገልጸዋል። እንደሚገመተውም፥ ከስልክም ሆነ መሰል ቁሳቁሶች ጋር የጠነከረ ቁርኝት መፍጠሩ ከእድሜ ጋር የሚያያዝ ነው። ወጣትነት ላይ ትስስሩ ከፍ ያለ ሆኖ፣ እድሜ በጨመረ ቁጥር እየቀነሰ ይሄዳል።

ከዚህም ባሻገር፥ ከመገናኛ ቁሶች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ቢደረጉም አጠቃቀምን በማስተካከል ረገድ ብዙም ለውጥ አይታይም። የዜንጦ ስልኮች ተጠቃሚዎች የትራፊክ አደጋን በማባባስ ረገድ ከጠጥቶ አሽከርካሪዎች ጋር ሊፎካከሩም ይችላሉ። ከዜንጦ ስልኮች ባሻገር ደግሞ በመደበኛው ተንቀሳቃሽ ስልክም፥ የጽሁፍ መልእክት በመላላክ ወቅት የሚደርሱ አደጋዎች ብዙ ናቸው። ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ከማድረስ ባሻገር፥ በራስም የሰውነት ጤና ላይ የሚፈጥሯቸው ችግሮች አሉ። ይህኔ ነው፥ ዜንጦ ስልክ ላይ የማኅበረሰብ ትስስር ገጾችን የመጠቀም ልምድ ሲጨመር “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” ማለት።

ፌስቡክ እንደምን ገነነ?

ከቤተሰብና ጓደኛ ጋር ተቀራርቦ የመኖር ፍላጎት፣ መዝናናት፣ ተመሳሳይ ፍላጎትና ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር ለመገናኘት መፈለግ ከፌስቡክ አግናኞች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር፥ የሰዎችን ተፈጥሯዊ የፉክክር ስሜት በማስተናገድ ረገድ የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች የሚጫወቱት ሚና ላቅ ያለ ነው። ሰዎች የለጠፉት ነገር ሰዎችን ማስደሰቱን መገንዘባቸው ብቻውን በራስ መተማመንን እና የእይታን ሁኔታ ከፍ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም፥ ሰዎች በመደበኛ ኑሯቸው ለማድረግ እየፈለጉ በጊዜ ማጣትና በኑሮ ዱብ ዱብ ሳቢያ ማሳካት ያልቻሉትን ነገር በማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች አማካኝነት ከውነዋል።

በፌስቡክ የተደረሱ ለቅሶና ሰርጎች፣ በፌስቡክ የተጠየቁ እስረኞችና ታማሚዎች፣ በፌስቡክ የተመረቁ አራሶችና ተማሪዎች ሞልተዋል። በፌስቡክ የጸደቁ ትዳሮችና ግንኙነቶችም አሉ። (እዚህ ጋ: ህንድ ውስጥ የሀይማኖት አባት ሙሽሮቹን ቃል አገባብተው፥ “እንግዲህ በይፋ ባልና ሚስት ሆነዋል” ሲሉ፥ ባል ቀልጠፍ ብሎ ስልኩን በማውጣት “ቆይ ፌስቡክ ላይ update ላድርገው” አላት የተባለችው ትዝ አለችኝ።) በርግጥ፥ አፈር ቆፍረን ችግኝ አልተከልንበትም እንጂ፣ ከቤት ተጠራርተን ወጥተን አጥር ተደግፈን አልሸናንበትም እንጂ፣ በአካል ተገናኝተን አልተንጫጫንበትም እንጂ፣ ድንኳን ጥለን አላስተዛዘንንበትም እንጂ፣ ምናምን ሸክፈን ታማሚና አራስ አልጎበኘንበትም እንጂ፣ ሰንበት ጠብቀን እስር ቤት ወይ ቤተ አምልኮ አልሄድንበትም እንጂ… ፌስቡክ ሰፈራችን ነው። ስንገናኝ በክፉ በደግ የምናነሳው መንደራችን ነው።

የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች ተደብቆ ለማውራት ምቹ ስለሆኑ በተለይ አይናፋሮች ይመርጧቸዋል። ማንነት ቢሸፈንም ሀሳቡ ከተሰማ ያው ማንነቱን ባለቤቱ ያውቀዋልና ነውርም ቢኖር አድናቆትም ቢኖር ይሰበስበው ዘንድ ባለበት ይሰየማል። ድረ ገጾቹ የእርካታ ምንጮችም ናቸው። እርካታውም ራስን በመግለጽ ልክ ይበዛል። ተቀባይነት በማጣት ልክም ይጫጫል። የሰዎች አመለካከትና ምላሽ ሁኔታም ብዙዎችን ያስጨንቃል። ፌስቡክ እኮ ሕይወት አይደለም ቢሉም የኑሮ አካል ሆኗል።

የማኅበረሰብ ትስስር ገጾች ጫናዎች

ሰዎች እርካታን ባገኙበት ልምድ ላይ የመቆየት ዝንባሌ አላቸው። ኀሰሳ እርካታን በሚደረግ ጉዞ ኪሳራን ማጨድም አይጠፋም። የበዛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህርይን በማበላሸት በኩል የሚኖረው አሉታዊ አስተዋጽኦ አለ። አንዳንድ ተጠቃሚዎች ሁለት ዓይነት ማንነት (double identities) ስለሚኖራቸው የፌስቡክ ማንነታቸውና የገአዱ ዓለም ማንነታቸው ይምታታል። ቅብ እና ወጥ ማንነቶች ይታያሉ። በጊዜ ሂደት፥ መምታታቱ ለራስም ተለምዶ ይታወቅና የባህርይ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናቶች ያሳያሉ።

ለራስ የሚኖር የተጋነነ ግምት፣ አሰልቺ የሆነ ራስን የመካብ አባዜ፣ የመደነቅ ያለመዘንጋት ፍላጎት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ  ትኩረት የመሳብ ፍላጎት በጊዜ ሂደት ስር የሚሰዱ ባህርያት ናቸው። ይህ ቀውስ ሲከሰትም፥ “ምን ልጻፍ” ብሎ መጻፍ፣  “ጓደኞቼ እዚህ ጉዳይ ላይ እንድናገር ይጠብቃሉ” ብሎ መብሰልሰል፣ “እነማን ምን አሉ? እኔስ?” የሚል ጭንቀት ውስጥ መግባት ይመጣል። ከልማድ ለመውጣት ቢፈልጉም ቀላል አይሆንም። በርግጥ እነዚህ ነገሮች ሁል ጊዜ ጎጂ ላይሆኑ ቢችሉም ማስተዋል ያስፈልጋል። ትችትን መቋቋም አለመቻል፣ መቀየምና ከሰዎች ውለታን መጠበቅ፣ ተያያዥ የጎን ጉዳቶቹ ናቸው። ይኽኔ ነው “እዩኝ እዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል” ብሎ መተረት።

የማኅበረሰብ ትስስር ገጾች አምባገነንነት (cyberbullying)ም አለ። ይሄ በብዛት ችላ ከመባል እና የጠበቁትን ምላሽ ከማጣት፣ አልያም በሌሎች ወዳጆች በተረጋገጠ ለራስ የተሰጠ ከፍ ያለ ግምት ሊፈጠር ይችላል። “እኔ እሻላለሁ፣ የእኔ እውነት ይበልጣል” ማለት ይቀሰቅሰዋል፤ ሰዎችን ቁልቁል የማየትና ጎራ ለይቶ የመዋል ነገርም ያባብሰዋል። በአጭሩ የ“እንደ እኔ ካልሆንክ ልክ አይደለህም” ውጤት ነው። ሌሎችን ሰዎች የማጥቃት ዝንባሌና ፍላጎት፣ የማንጓጠጥ ልማድም በሂደት ግንኙነቶችን ያሻክራል። ሌላውን ስንሰድብ ያየና የሰማ፣ “ትናንሽ መንግስትነታችን”ን ያስተዋለ ሰው “ጓደኛህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ” ብሎ መሸሹን ይመርጣል። መላመድ አስሮት አላራምድ ካለው ደግሞ እርግጫችንን እና ግልምጫችንን እያስተናገደ ይኖራል። ይህኔ ሌላ ዓይነት ቀውስ ይፈጠራል።

ማኅበራዊ ንጽጽሮች

ሰዎች እንዴት ማሰብ፣ ምን ማንበብ፣ ምን መናገርና ምን ዓይነት ጽሁፎችንና ፎቶዎችን ማጋራት እንዳለባቸው ለማወቅ ሌሎች ሞዴል የሚያደርጓቸው ወዳጆች ይኖሯቸዋል። “ሰዎች ምን ይላሉ?” ይባላል። አንዳንዴ የሚወራ ሲጠፋ፥ “እነ እከሌ ያሉትማ…” ብሎ ርዕሶችን ካለእውቀትና በቂ ፍላጎት የመቀላቀል ልማድም አለ። በዚህም የተነሳ፥ አንዱ ግድግዳ ላይ ውሀ ከተወቀጠ፣ ሌላው ሁሉም ሰው ግድግዳ ላይ ውሀ ይወቀጣል። አንዱ ግድግዳ ላይ ድንጋይ ሲፈለጥ ሰፈሩ ሁሉ ድንጋይ ፈላጭ ነው። (አንዷ ሴት እንጀራ ስትሸጥ፣ ሰፈሩ ሁሉ እንጀራ ሻጭ ሆኖ፣  አዲስ ጉሊት እንደሚቋቋመው ዓይነት።)

ደፈር ብሎ የራስን አቋም እና እምነት ከማስቀመጥ ይልቅ፣ የሰዎችን ዱካ ስንከተል ድረ ገጾቹ ከተገነቡበት ዓላማ ውጭ ሱስ ውስጥ ተዘፍቀን የምናተርፈው ጊዜና ገንዘብን መግደል ይሆናል። የራስ እውነትና እምነት ተሽቀንጥሮ፥ ‘ልክ’ ለመባል ብቻ የሰዎችን ሀሳብ ማስተጋባት ይበረታል። ርካሽ ተወዳጅነት ቢኖር እንኳን ካልዘለቀ ርካሽነቱ ወሰን አይኖረውም። ከዚህም ባሻገር ሌሎች ሰዎችን እየተመለከቱ ራስን በጸጸት መግረፍና በማይታወቅ ዓይነት አለንጋ ማሰቃየትም ይጀመራል። ይህም ራስን ለማሳደግ መነቃቃትን ይገድላል። – ሌላ ዓይነት ቀውስ ይቀሰቀሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን፥ በበጎ መነሳት የሚገባቸው የሚያነቃቁ የንጽጽርና የፉክክር ስሜቶችም አሉ። የሰውን ስኬት ሲያዩ የራስን ስኬት ቢናፍቁና ለእርሱ ደፋ ቀና ብለው እንደዚያኛው ሰው መሆን ቢችሉ የሚደነቅ ነው። ለምሳሌ፥ አንድ ሰው ባነበበው መጽሐፍ ተደንቆ ከመቆጨትና ራስን ከመቅጣት፣ መጽሐፉን ርዕሱን ጠይቆ ለማንበብ መጣር ያሻሽላል። ሰዎች ስለእኛ የሚያስቡትንና የሚጠብቁትን ዓይነት ኑሮ እንኑር ስንል ግን፥ በራስ መተማመንን ቀስ እያለ ይሸረሸርና ቲማቲም “አትልክት ነኝ? ወይስ ፍራፍሬ?” የሚል ውዝግብ ውስጥ ገባች እንደተባለው እንሆናለን።

ለምን ይዋሻል?

በንጽጽር ፍላጎት የተነሳ ያልሆኑትን ሆንኩ ብሎ የመግለጽ አባዜም አለ። ብዙ የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጽ ማንነቶች የተፈጠሩ ናቸው። የእረፍት ቀኑን በማይፈልገው መልኩ ያሳለፈ ሰው፥ ሰኞ ማለዳ ስለ እረፍት ቀናቱ ውብነት ሊተርክ ይችላል። ስራ ቦታ “ምን ዓይነት ቀን ነው” ብሎ እያማረረ ውሎ፣ ወደ ፌስቡክ ላይ “ቀኑ ደስ ሲል” ይላል። በሕይወታቸው በምስቅልቅል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንደ ደስተኛ ነዋሪ አድገው ያወራሉ። አብረው እየኖሩ አባቱ ትዝ ብለውት የማያውቅ ሰው ‘ዓለማቀፍ የአባቶች ቀን’ን ጠብቆ “አባቴ…” ብሎ ጀምሮ በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ፣ እጅግ የሚያስቀና ልጅነትና ወላጅነትን ያወራል።

ታዲያ እንዲህ ባለ ወቅት ነው ንጽጽር የሚጎዳው። ታማኝ ሆኖ ለመኖር የሚጥር ሰው በውሸታሙ ሰው ሕይወት ቀንቶ ራሱን ሊጎዳና እድሉን ሊያማርር ይችላል። እርሱ እየዋሸ የሚኖር ቢሆን እንኳን፥ እውነቱን ልቡ ያውቀዋልና በሌሎች ሰዎች ውሸቶች የራሱን እውነት ያነጻጽራል። ‘እነሱም ዋሽተው ቢሆንስ’ ብሎም አያስብ። በጣም የሚያሳዝነውም ሰዎች ራሳቸውን የሚጎዱትና ድብታ ላይ የሚወድቁት በተፈበረኩ ማንነቶችና ወሬዎች የተነሳ ነው።በሂደትም ለራስ የነበረ ጥሩ ግምት ሊያሽቆለቁል ይችልና ገዢም ቢለምን የማይሸጡ የማይለወጡ መሆን ይመጣል። – ይህም ሌላ ቀውስ ነው!

ኧረ አንቺስ ቅሪብኝ” vs “ካላንቺ አልኖርም 
(‘hard to live in, and hard to live out’)  

“ሰለቸኝ” ብለው ከፌስቡክ ዞር ሲሉ፥ ቅር ቅር ማለትም የተለመደ ነገር ነው። እንኳን ተሰናብተው ሄደው ላፍታ ወጣ ብለው ሲቆዩ እንኳን፥ መንግስት ተገልብጦ ታምር ተሰርቶ የሚጠብቅ ይመስላል። በዚህ የተነሳም ሰዎች ከፌስቡክ ዞር ሲሉ ድብርት እንደሚጫጫናቸውና ቶሎ እንደሚመለሱ ይናገራሉ። (ይህም ቀውስ ነው!) እና የጨዋታው ደንብ ወጣ ገባ ይሆናል። የማኅበረሰብ ትስስር ድረ ገጾች ላይ ብዙ ሰዓት በቆየንና ከብዙ ሰዎች ጋር ባወራን ቁጥርም የእኛ ሕይወት በሌሎች ሲለካ ምንም እንደሆነ የመሰማቱ ነገር ይጠነክራል።  በአንጻሩ፥ የራስን ማንነት፣ ውሎዎቻችንን፣ ልምዶቻችንን እና ፍላጎቶቻችንን በአግባቡ በመግለጽና የሰዎችን ሕይወትም በመጋራት ከተጠቀምንበት ግን፥ ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ እናደርግበታለን።

ከፌስቡክ ርቀው ሲቆዩ ድብርት ቦታውን ይረከባል። ሲመለሱም ያው ሌላ ዓይነት ድብታ አያጣም። እዚያ በቆየንበት ጊዜም፥ “ኧከሌ ዘጋኝ” “ኧከሊትን አስቀየምኳት” እያሉ የሚጨናነቁትን ያህል ከዚያ ሲርቁ “ኧከሌ ናፈቀኝ” “ምን ተወራ ይሆን” በሚል ጭንቀት ይተካል። ያልተጻፈውን የማኅበረሰብ ድረ ገጽ ማኅበራዊ አኗኗር ህግና አካሄድ እንደሳትን ሲሰማን፣ ፌስቡክ ላይ የምናሳልፈው ጊዜ እንደከሰረና በከንቱ እንደባከነ ስናስብ፣ አጠቃቀማችን ባለመገራቱ የተነሳ የጭንቀትና እንቅልፍ ማጣት ሲፈጠርብን፣ ከወጡ በኋላ የሚኖር ጸጸት (post logout regret) ሲጠዘጥዘን፣ ማንነታችን እንደተጎሳቆለ እና የገአዱ ዓለም ወዳጅነቶቻችን እንደሻከሩ ስንረዳ፣ በኢንተርኔት ወጪ የተነሳ የቁጠባ ባህላችን ከስሩ መድረቁን ስናስተውል… ዞር ይባልና፣ ደግሞ ሱስ ይጎትታል። ይህም ቀውስ ነው!

ታዲያ ምን ይሻላል?

የማኅበረሰብ ድረ ገጾችን የአጠቃቀም ልምዳችንን ብናሻሽል የገአዱን ዓለም ጉድለቶቻችንን በመሙላት የበለጠ አትራፊ ያደርጉናል። ጓደኞቻችንን እና የምንሳተፍባቸውን ርዕሶች በመምረጥ፣ የምንቆይበት እያንዳንዱ ደቂቃ በጊዜና በገንዘብ ቢተመን ዋጋ እንዳለው በማወቅ ቆይታችን ራስንም ሰዎችንም በማሳነስ ላይ ያተኮረ እንዳይሆን በመጠንቀቅ፣ ምስጢር ጠባቂነትን እና የመረጋጋትን ሁኔታ በማሻሻል፣ የራሳችንን ፍላጎቶች ለይተን በማወቅ የሌላውን ለሌላው በመተው፣ ከሚረብሹን ለመራቅ ‘unfollow’,  ‘unfriend’, ‘block’ የተባሉ አማራጮችን በመጠቀም… እያጋራን እና እየተጋራን እርካታችንን እናብዛ።

ሰላም!

P.S. ይህ ጽሁፍ በአዲስ ገጽ መጽሔት ቁ 01 ቅጽ 01 እና 02 በሁለት ክፍሎች ታትሞ የነበረ ነው። አዲስ ገጽ መጽሔት በየሁለት ሳምንቱ የሚታተም ሲሆን፥ ቀጣዩ እትም ቅዳሜ ታህሳስ 23/2008 ዓ/ም ለንባብ ይውላል። ላለፉ እትሞቹ ድረ-ገጹን ይጎብኙ።