ትውስታ… (አብደላ ዕዝራ)

13394118_1346035022079626_8563230783627582053_n“ጥሬ ሁል መብቀያ፣ መብሰያ ጊዜ አጣ፤
‘ካፍ ካፍ የሚለቅም’፥ የሰው ዶሮ መጣ።”
ብዬ የዛሬ ሶስት ዓመት የለጠፍኩት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን ሀያሲ እና ፀሐፊ ጋሽ አብደላ ዕዝራ አስፍሮት ከነነበረው አስተያየት ፌስቡክ አስታወሰኝ። አስተያየቱን ከስር አስፍሬዋለሁ። ትንሹን ነገራችንን በቁምነገር መዝግበው እንደትልቅ እየቆጠሩልን የሚያበረቱንና የሚገስጹን ይብዙልን!
* * *
“ቀለማቱን ብቆጣጥር፥ ቤቱን ባስዉብ ባሰማምር፥
ቅኔ ዘረፋ ብማስን፥ ወርቁን ከሰሙ ብጋግር”… ያልከዉ ትዝ አለኝ።
“የብርሃን ልክፍት” እንደ ርዕስና ሽፋን የሚመጥነዉ የለም። ደበበ ቀድሞህ “የብርሃን ፍቅር”፥ አለማየሁ ገላጋይ ለጥቆ “የብርሃን ፈለጐች” ቢሉም፥ እንደ ርዕስ የልክፍትን [የብርሃን ልክፍት] ምትሃት ++ ያዉ እንደመጥምቁ በምናብ ወንዝ ተነክሮ ይሆናል። ጀርባዉም ይነባባል። ጨለማዉን ገምሶ የሚያንሰራራ የብርሃን ልክፍትአይለቅም።
የገዛሁት ሁለተኛዉን ዕትም ነበር። Oland በድሎሃል… ዉስጡን ለቄስ አስመሰለዉ፤ ግጥሞቹን ማለቴ አይደለም። scan ወይም ቀሺም ፎቶ ኮፒ መሰለ፤ በስንኝና በለጣቂዉ መካከል የተረሳዉ/የረገበዉ ክፍተት ገፀ ዉበቱን አደበዘዘዉ። የተፃፈበት ሆሄ ቢነበብም ቀለሙ [ካንተ ልዋስና] ወየበ። ሊትማንን “ገንዘቤን መልስ” አልለዉ-ጥቂት ግጥሞችህ እንቁ ሆነዉ ማን በፍራንክ የለዉጣቸዋል?
የመሰጠህን አንድ መንቶ ምረጥ በለኝ [] ሶስት ገፅ የወረረዉን የግጥሙን ድባብ የሚያባንንም፥ የሚያስተክዝ ነዉ። ተስፈንጥሮ የወጣ መንቶ አለ።
““እንኳን አደረሰህ” ከተንኳኳ በሬ
ያን ጊዜ እነቃለሁ፥ እሱ ነዉ ሀገሬ”
የተወሰኑ ግጥሞች ደግሜ የማነባቸዉ አሉ፤ ጥቂት የተንዛዙ እንደ መስለምለም ይከጅላቸዋል። ከመሰጠኝ አንዱ አሁን የሚታወሰኝ አጭር ግጥምህ ናት- “ፍርሃት” የምትለዉ። ለምን? እንዴት? ሰለመፅሐፍህ በሌላ ወቅት ሂስ መስል የተሰማኝን እገልጥለሃለሁ።
አሁን “ወርቁን ከሰሙ” የጋገርክበትን ከላይ የለገስከንን ዕምቅ መንቶ ልነካካዉ። አሻሚ ነዉ። ብርሃኑ ገበየሁ እንደሚለዉ “አሻሚነት ከአንድ ፍቺ በላይ ትርጓሜ መያዝ፥ ከግጥሙ ዐዉደንባብ በመነሳት ቁርጥ ያለ ትርጓሜ ለመስጥት አለመቻል” ነዉና እንደ አንባቢዉ ይነባበራል። ሁል ገድፈህ ሁሉ ቢሆን ዜማዉን አይጣረስም፤ ቀለም ሳይቆጠር እንዲሁ ሲደመጥ ያስታዉቃል። አለበለዝያ የ-ሁል- አደናጋሪነት የስንኙን ጠብታዎች ሊያመከን ነዉ።የተደራሲዉንም ትኩረት ይሻማል።
ገና እንደ አነበብኩት አዞ ትዝ አለኝ – አዞ እንባነቱ አይደለም – ሰፊ አፉን ከፍቶ ከጥርሶቹ መካከል አእዋፍ ጥሬ ስጋዉን ሲያስለቅሙ፤ ለአዞ እፎይታ ለነሱ መሰንበት። ይህ አንድምታ ነዉ።
“ካፍ ካፍ የሚለቅም የሰዉ ዶሮ መጣ” ግን ጉዳቱ ያሳስባል። አንድ የጥሬ ትርጉም “ያልተነካ ፥ አዲስ” ከሆነ አድገዉ ለወገን ምርኩዝ የሚሆኑትን ካከሰማቸዉ፥ በዘራፊ ማን ይመካል? ካፍ [ካፌ ባይሆንም] ከቀኝ ቢነበብ ፍካ ፍካ ሰለሚሆን ጮርቃዉን ብቻ አይደለም የፈካዉንም ሊለቃቀመ እንጂ። ይህ በደሉን አባባሰዉ። ከቀኝ ወደ ግራ ባይነበብም ሰሙ ወደ ወርቅ ሲመራም ነዉና ይነበብ።
ከጀርባዉ ከተስተዋለ ግን ብርቅ አንድምታ አለዉ። ዶሮ ጥሬ ለቅማ እኮ ነዉ [የአዳም ረታ ገፀባህሪይ – መዝገቡ- በልቶ የተደነቀበትን] የዕንቁላል ፍርፍር የምናገኘዉ። ጥሬ ተለቅሞ የሚጥም ከመቋደሻ እስከ ፈረሰኛ ለፋሲካ ወደ ብርሃነ ትንሳኤዉ የምንሻገርበት። “የሰዉ ዶሮ” የላመዉን፥ ያልሰለጠነዉን እየለቃቀመ እንደ ዕንቁላል እንደ ጫጩት ሊቀፈቅፋቸዉ ከቻለማ እሰየዉ ነዉ።
የግጥምህ አሻሚነት እየቆየ መዘርዘር፥ መነስነስ ይጀምራል። ይልቅ አሁን የመስፍን አሸብር ምጥን ግጥም ታሰሰኝ፤ በሱ ተመሰጥና ይብቃን።
“ጫጩቶቿን ብላ
ጭራ ልታበላ
“ቋቅ! ቁቅ!” እያለች፥
ይዛቸዉ ራቀች
ሄደች ኰበለለች፤
ያረባኋት ዶሮ
እንደወጣች ቀረች።”
—— // ——
ሀያሲ እና ፀሐፊ አብደላ ዕዝራ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ/ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን። ለኢትዮጵያ ስነጽሁፍ እድገት ትልቅ ሀብት ነበር።

ነፍሱ በሰላም ትረፍ!

ፍቅር ጥላ ሲጥል

580467_429737607114330_1388661574_nበገና
ቢቃኙ፡
ሸክላ
ቢያዘፍኑ
ክራር
ቢጫወቱ፡
ለሚወዱት
ምነው
ሙዚቃ
ቢመቱ
ቢቀኙ
ቢያዜሙ
ቃል
ቢደረድሩ
ጌጥ
ውበት
ቢፈጥሩ
ቤት
ንብረት
ቢሠሩ
አበባ
ቢልኩ
ደብዳቤ
ቢልኩ
ምነው
ቢናፍቁ !
አገር
ቢያቋርጡ 
ቢሔዱ
ቢርቁ
ዓመት
ቢጠብቁ
ዘመን
ቢጠብቁ።
ለሚወዱት ምነው ?!
 
/ገብረክርስቶስ ደስታ/