እንደወረደ! ;)

የቤቲን እና የዶ/ር ደሳለኝን ቃለ መጠይቁን አየሁት። የተባለውን ያህል የተጋነነ ሆኖ ግን አላገኘሁትም። ደሳለኝ አለመዘጋጀቱ ያስታውቃል። መዘጋጀት ሲባል፣ ለቃለ መጠይቅ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ እንደ ፓርቲ አመራር ራሱን በብዙ ነገሮች ውስጥ ማለማመድ እና ነጥሮ የወጣ ሀሳብ/መልስ የሚሆን ነገር ማዘጋጀት ነበረበት። አባላቱም እንዲሁ ማድረግ ነበረባቸው። ለከእንግዲውም መዘጋጀት አለባቸው።
 
በዋናነት ደሳለኝን የማይሆን ነገር ውስጥ የከተተው ጋሻው እና ክርስቲያን የተባሉ ስራ አስፈጻሚ አባላቶቹ ያደረጉትን ያልተገባ እና ያልበሰለ ንግግር ለማስተባበል እና “ማለት የፈለጉት” እያለ፣ ያላሉትን ሊልላቸው እና ያሉትን ሊያለባብስላቸው ባደረገው ጥረት ነው።
 
ከዚህ የምንማረው/የምንረዳው፣ አባላቱ (እንዲሁም ሌሎቻችን) ከፌስቡክ ወጣ እያሉ ወደ መጽሐፍት ገጾች አየት ማድረግ እንዳለባቸው ነው። እሱም ዐይኑን ያፈጠጠ፣ ጥርሱን ያገጠጠ ነገርን በይቅርታ ማለፍ ቢችል ተወዳጅነት እንደሚጨምርለት ከዶ/ር አብይ ኢህአዴግ መማር ይቻላል።
 
አብን ገና የሶስት ወር ጨቅላ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ክፍተቶች ቢታዩ ብዙም ባያስደንቅም፣ ችኩል ችኩል እያሉ የፈጠሩትን ስህተት፣ “ሌላው ሰው ካለበት የመረዳት ችግር የተነሳ ነው እንጂ እኛ ልክ ነን” ማለት ወዳጅ እና ደጋፊ ያሳጣል እንጂ ሩቅ አያስኬድም። ከአሁኑ ያልተጀመረ ይቅርታ የመጠየቅ እና ራስን የማረም ባህልም፣ ውሎ አድሮ ስለመቀጠሉ መተማመኛ አይሰጥም።
 
ነገሮች በግልጽ ለክርክር እና ቅሬታ ክፍት በሆኑበት ቦታዎች/ሁኔታዎች “ስህተት ነበር። ይቅርታ። እንዳይደገም እንመክርበታለን።” ብሎ ማለፍ እየተቻለ፣ ባስረዳው ቁጥር የማይሆን ነገር ውስጥ ራሱን ከቷል። በዚህም፥ ከ27 እስከ 48 ደቂቃ ያለው ጊዜ በከንቱ እና ራሱን በማሳጣት የባከነ ነው። ልክ እንደዒድ በዓል መልካም ምኞት መግለጫው “ሌላን ሰው ካስከፋ ይቅርታ” ብሎ በሰላም እና በክብር አልፎት፣ ሀሳቦቹን ማስረጽ እና ሀሳብ ላይ ማውራት ይችል ነበር።
 
ደሳለኝ ምናልባትም ፓርቲውን (የፓርቲውን ስም) ለማስተዋወቅ ያህል ጥሩ እድል አገኘሁ ብሎ የሄደ ዓይነት ይመስላል። እሱ ደንገጥ ሲል እሷ በስሜታዊነት እየተናጠች ኮስተር ማለት መጀመሯ ነጻ ጋዜጠኛ የማያስብላት ነው። ጭራሽ ልትቆጣው ሁሉ የሚያምራት ቦታ አለ። ደካማ ጎን ያገኘች እየመሰላት፥ የልብ ልብ እየተሰማት፣ እንደ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ለመሆን የፈለገችባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው።
 
እንደ ቃለመጠይቅ አድራጊነቷ እውነቱን እና ሀሳቡን መፈልፈልና ማውጣት ላይ እንጂ፣ የእሷን ሀሳብ ወይም መከላከያ እና ቅሬታ ማከል ላይ ማተኮሯ ለመደበኛ ቃለመጠይቅ የሚያስኬድ አይመስለኝም። ያም ሆኖ ግን፣ እንደፈለገች አድርጋ መጠየቅ መብቷ ነው። ሊያሰድባት የሚያደርስ ነገር የለም።
 
የተከፋ ሰው፥ ፕሮግራሞቿን አለመስማት፣ ወይም ደግሞ እሷ ጋ ቃለ መጠይቅ አልደረግም ብሎ ሊያምጽ ይችል ይሆናል፣ እንጂ “ሊቀመንበሬን ይህን ጠየቅሽብኝ፣ አጨናነቅሽብኝ” ብሎ የተሳደበ አባል ወይም ደጋፊ፥ እድሉን ቢያገኝ ልሰር ልግረፍ ማለት አያምረውም አይባልም እና “ሳይቃጠል፣ በቅጠል!” ነው መሆን ያለበት።
 
በየመሀሉ እየገባች በተነሳው ነገር ላይ ሁሉ ከኦሮሞ ጋር ማነጻጸሯም በአስፈላጊ ቦታ የሆነ አይደለም። ራሷንም ወደ ኦሮሞ ብሔር ያዘነበለች አድርጎ ያሳያታል።
 
ነገሬ ብላ ፓርቲውን ማሳጣት ላይ ወይም ራሷን እነደሀይለኛ ማስቆጠር ላይ ማተኮሯን የሚያሳይ፣ መሀል ላይ በቃለመጠይቁ ወቅት ያለተጠቀሰ እና ካለደሳለኝ እውቅና የተሰነቀረ የልማታዊ አርሶአደሮች ምስል አለ። በመንግስት የሚደገፈው የአማራ ክልል ቴሌቪዥን (መቼቱ አልተጠቀሰም) ለፕሮፖጋንዳ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ እንደማስረጃ መሰንቀሯ ሳያንስ፣ እሱ ተመልክቶት ምላሽ እንዳይሰጥበት ማድረጓ የሙያን ስነምግባር ያጓደለ መሰለኝ።
 
ደሳለኝም ቢሆን “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ፣ እሷ በጀመረችው ማነጻጸር ገብቶ ‘ፓርቲው የተቋቋመው፣ እና የምናደርገውን ሁሉ የምናደርገው ሌሎች ስላደረጉት ነው’ ዓይነት ገደምዳሜ ላይ እንድንደርስ የገፋፋን ይመስላል።
 
የአማራ ፓርቲ ሊቀመንበርነት፣ ፓርቲው ለመደራጀት ገፊ የሆነውን ምክንያት የስሙን ያህል፣ በጥናት እና ንባብ ተደግፎ አጣፍጦ ማስረዳት ይጠበቅበታል/ት ነበር። ቢያንስ ስለፕሮግራም ሲጠየቅ መደናገጥ የሚጠበቅ እና አስፈላጊ አልነበረም። እንጂ፣ ቢያንስ አማራ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ያበረከተውን ነገር ለመጥቀስ፣ ስነጥበቡን እና ኪነ ጥበቡን መጥቀስ ብቻውን ይበቃው ነበር።
የእድገት እና የስልጣኔ ጠቋሚ የሆኑትን የወሊድ ቁጥር መቀነስ እና ተያያዥ ዴሞግራፊክ ነገሮችን፣ እንደበደል ማቅረቡም ከምሁርነቱ አይጠበቅም። ከዚያ ይልቅ በቅርቡ እንኳን በአማራ ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡትን የእስር ቤት አያያዝ ፕሮግራሞች ጠቅሶ መናገር ይችል ነበር።
 
የአካባቢውን የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በጊዜ መዳርን ጨምሮ ሌሎች ልማዳዊ ድርጊቶች ያበረከቱትን አስተዋጾ፣ ት/ት እንዳይስፋፋ እና መሰረተ ልማቶች እንዳይከናወኑ በመደረጉ የደረሱትን ጥፋቶች፣ እንዲሁም ብዙ መውለድ ለመቀንጨር የሚያድርገውን አስተዋጽኦ እና ያም የሚያመጣውን የአእምሮ ውሱንነት ማሰብና፥ ጉዳዩን በተሻለ ማስረጃ ማቅረብ ነበረበት።
 
ወይ ደግሞ እንደ ኢህአዴግ/ብአዴን፥ ፓርቲው ዋና ዒላማ ያደረገው ገበሬውን ሆኖ፣ በአሉሽ አሉሽ እንፍሽፍሽ ማለፍ ፈልገው ይሆናል።
 
በዚህ የተነሳ፣ ማህበረሰቡ ሊደነቅበት በሚገባው ነገር ክስ ማጠናከሪያ አድርጎታል። (ልክ መስታወት ሲሰበር ይቆርጣል፤ ካዩበት ያሳያል እንደማለት ያለ፥ ነገሩን ከብዙ አንግል ማየት እና ትክክለኛ መከራከሪያ ማቅረብ ይቻላል። እኔ እንኳን ከሱ የተሻለ ይህንን ጉዳይ ማስረዳት የምችል ይመስለኛል።)
 
እሷም ጉዳዩ ላይ ንባብ ጠገብ ብትሆን ኖሮ፣ እዚህ ጋር ጥሩ ውይይት ያደርጉ ነበር። ባይሆን ግን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ሪፖርቶች ላይ የአማራው ቁጥር አንሶ እንዲዘገብ የሚደረግበትን ምክንያት ማህበረ ፖለቲካዊ አድርጎ ማቅረብ እና ነጥብ ማስያዝ ይችል ነበር።
“በአብን ስም ያልተገባ ነገር የሚያደርጉ ስላሉ፣ ግለሰቦች ስለሚጽፉት ነገር ፓርቲው ሊወቀስ አይገባውም” ዓይነት ነገር ባለበት አንደበቱ፣ ስለእነ ግንቦት 7 ሲናገር ርግጠኛ ሆኖ “ደጋፊዎቻቸው” አባባሉም ከወገንተኝነት ያልጸዳ አቋም እንዳለው ነው የሚያሳየው።
 
ደግሞ በአብን ስም ለተደረጉ ስህተቶችስ፣ ፊት ለፊት ቀርቦ የእኛን ፓርቲ አይወክልም ብሎ ወዳጅንም ማረጋጋት፣ ጠላትንም ማስደንገጥ አይቻልም ወይ? ወይስ እንደ ኦነግ ሰው ተገድሎ፣ ሰው ተባሮ “አባላቶቼ አይደሉም። በስሜ ነው ይህን የሚያደርጉት።” ለማለት ነው የሚጠበቀው?
 
ሲመስለኝ፡
 
የአብን ነገር እንደ ትኩስ ሽልጦ “ጠዋት ተመርቶ፣ ከሰዓት መርካቶ” ዓይነት ይመስላል። ምናልባትም ዋና ግብ ያደረጉት ለመጪው ምርጫ መሳተፍ ነው።
 
የምር ለአማራው የሚቆረቆሩ ከሆነ ግን ከሕዝባዊ ስብሰባዎች እና ውይይቶች እኩል፣ ውስጣዊ ውይይቶች፣ የንባብ እና የርስበርስ ስልጠና፣ የመጽሐፍ ተዋውሶ ማንበብ ዝግጅቶችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ያድርጉ አያድርጉ ባላውቅም ከሚናገሯቸው እና ልዩነትን ከሚይዙባቸው ነገሮች ተነስተን፣ ክፍተት እንዳለ በግልጽ መናገር ይቻላል።
ነገሩን ጠቅለል ስናደርገው፡
 
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አብንን ሳይወክል፥ ስለአብንም ሆነ አማራ መደራጀት ቢጠየቅ ከዚህ የተሻለ ቃለመጠይቅ ማድረግ ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ! ይህም የሚሆነው ከእርጋታ እና ነገሩ ላይ ከመብሰል እንጂ፣ ከግል አቅም አይደለም። ዶ/ር ደሳለኝ እርጋታውን እና ቅንነቱን አሳይቷል።
አብን እንደሶስት ወር ዕድሜው በጣም ጥሩ እየሰራ ነው! እንደ አማራ ሕዝብ ግን ገና ነው! ለሰፊው እና ስልጡኑ አማራ ሕዝብ አብን ይጠበዋል።
 
ባልተያያዘ ወሬ ደግሞ፡
 
እሱ “አብን ለሕብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ስጋት ነው” ያላትን ወስጄ፥ ሕብረ ብሔራዊው ግንቦት 7፣ ለአብን ስጋት እንዳይሆን እንደሚፈሩ፤ አባላቱም በዚህም ስጋት የተነሳ ግንቦት7ን ማጥላላት ላይ እንደተጠመዱ ብነግረው አልጠላም።
 
በቅንነት ተደራጁ! የተደራጃችሁም በቅንነት ተራመዱ! በርቱ!
ሰላም!